Fana: At a Speed of Life!

ለጥምቀት ወደጎንደር ለሚመጡ ጎብኚዎች ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎች ተዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጪው የጥምቀት በዓል ወደጎንደር የሚመጡ ጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች መዘጋጀታቸውን የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷የጥምቀት በዓል የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃትና የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰሱ ቅርሶች መመዝገቡን ያስታወሱት ሃላፊው÷ ይህን ሃይማኖታዊ በዓል ለከተማው የቱሪዝም ገቢና የኢኮኖሚ እድገት ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለበዓሉ ወደከተማው የሚመጡ ቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም በከተማዋ ያሉ የመስህብ ሥፍራዎችን፣ በጎርጎራና በጣና ሐይቅ ደሴቶች እንዲሁም በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የጉብኝት መርሐ ግብሮች አንስተዋል፡፡

የአካባቢው ጸጋ የሆነውን የአዝማሪዎች የቀደመ ባህላዊ እሴት ለማስተዋወቅ የሚያስችል የአዝማሪዎች ፌስቲቫል ከጥምቀት በዓል አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

የአካባቢውን ባህል፣ ወግና ትውፊት ለቱሪስቶች ለማስተዋወቅ የባህል ሳምንት እንደሚዘጋጅ ጠቁመው÷ በዚህም የጎዳና ላይ የባህል አልባሳት ውድድር ከማድረግ ባለፈ ባህላዊ ቁሳቁስ፣ የጋብቻ ስርዓት፣ የፀጉር አሰራር እና ሌሎች ትይንቶች ይቀርባሉ” ብለዋል።

በዘንድሮ የጥምቀት በዓል የአካባቢውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት በስፋት በማስተዋወቅ ከ700 ሺህ በላይ ቱሪስቶች ጎንደር ከተማና አካባቢው የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ይህም በኮቪድ-19 እና በነበረው ጦርነት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪስት ፍሰት ወደነበረበት እንዲመለስ ከማድረግ ባሻገር የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግና የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በመጪው ጥር ወር የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ስኬታማ ለማድረግ እንዲቻል በከተማ ደረጃ አንድ ዐቢይ ግብረ ሃይልና 9 ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.