Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ይሸፈናል – የክልሉ ግብርና ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚሸፈን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በዛሬው ዕለት የበጋ መስኖ ስንዴ የዘር ማስጀመርና የቡቃያ ጉብኝት በማዕከላዊ ጎንደር ምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ተጀምሯል።

በጉብኝት መርሐ ግብሩ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው÷በክልሉ ለበጋ መስኖ ስንዴ ከ265 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መለየቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም 165 ሺህ ሄክታሩ መታረሱን የገለጹት ሃላፊው÷ 60 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም ጠቁመዋል፡፡

በአካባቢው ሰፊ ህብረተሰባዊ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጎንደር ቀጠና ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት አርሶ አደሮቹ እንዲያለሙ የቁሳቁስና ሙያዊ ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።

ዩኒቨርሲቲው ለበጋ መስኖ ልማቱ የማዳበሪያ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ፥ አራት ትራክተሮችንና አንድ ኮምባይነር ወደስራ ማስገባቱም ተገልጿል፡፡

አርሶ አደሮቹ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ፥ ባለፈው ዓመት ካዩት አመርቂ ተሞክሮ በመነሳት በተያዘው የምርት ወቅት መሬታቸውን በዘር መሸፈናቸውን ገልፀዋል፡፡

ከዚህም ሰፊ የስንዴ ምርት እንደሚጠብቁም ነው የተናገሩት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.