Fana: At a Speed of Life!

ታግቻለሁ በማለት ከባለቤቷ ገንዘብ የጠየቀችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች

አዲስ አበባ፣ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀሰት ታግቻለሁ በማለት ባለቤቷ 150 ሺህ ብር እንዲያስገባላት የጠየቀችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሏን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ወንጀሉ የተፈፀመው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ሰርጢ ማርያም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን ተጠርጣሪዋ ለባለቤቷ ስልክ በመደወል እንደታገተችና 150 ሺህ ብር እንደተጠየቀች ትገልፅለታለች፡፡

ግለሰቧ ገንዘቡን በራሷ የንግድ ባንክ አካውንት ገቢ እንዲያደርግላት እና ካላስገባላት ግን ያገቷት ሰዎች ሊገድሏት እንደሚችሉ ነግራው ስልኳን ትዘጋለች፡፡

በድጋሜ በመደወልም የተባላችሁትን ገንዘብ በአስቸኳይ አስገቡ በማለት ግብረ አበሯ ባለቤቷን እንዲያወራው ማድረጓን ፖሊስ ገልጿል።

ባለቤቷም ጉዳዩን ተጠራጥሮ ለፖሊስ ያመለከተ ሲሆን ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ ሲያሰባስብ እና ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ግለሰቧ እንዳልታገተች እና መንገድ ላይ ስትንቀሳቀስ እንደታየች አረጋግጧል፡፡

ጥቆማውን መሰረት በማድረግ ፖሊስ ባደረገው ክትትል በዚያው ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ሸገር ህንፃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ዘመድ ቤት ውስጥ ተደብቃ በቁጥጥር ስር አውሏታል፡፡

አባሪ ተባባሪ በመሆን በዚህ ወንጀል ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሌሎች ሁለት ግለሰቦችም ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.