Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከቻይና የተሰጣትን ከቀረጥ ነጻ ምርት የማስገባት ዕድል አሟጣ ልትጠቀምበት ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከቻይና የተሰጣትን ከቀረጥ ነጻ ምርት የማስገባት ተጨማሪ ዕድል አሟጣ ልትጠቀምበት እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

በንግድና ቀጣዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ቁምነገር እውነቱ ፥ ኢትዮጵያ 1 ሺህ 644 የምርት ዓይነቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ግዛቷ እንድታስገባ ቻይና ተጨማሪ ፈቃድ መስጠቷን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ቻይና ፈቃዱን ለኢትዮጵያ ያሳወቀችው ታኅሣሥ 3 ቀን 2015 ዓ.ም.መሆኑን እና የምርቶቹ የክብደት መጠን፣ የሚላኩበት ጊዜ እንዲሁም እስከ መቼ ድረስ የሚቆይ ዕድል ነው የሚለው አለመገለጹን አስረድተዋል፡፡

በምርቶቹ ልየታ፣ ዝግጅት እና አላላክ ላይ እንደሀገር መንግሥት የሚያስቀምጠው አቅጣጫ እንደሚኖር ይጠበቃል ያሉት ወይዘሮ ቁምነገር፥ ከዚህ ዕድል ኢትዮጵያ በሙሉ አቅሟ እያመረተች የምትልካቸው ምርቶች ላይ የበለጠ ተጠቃሚ እንደምትሆን አመላክተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በወጪ ንግድ ለሚከታተላቸው 15 ዋና ዋና ተቋማት ዕድሉ ከተሰጠን ዝርዝር ውስጥ የሚያመርቷቸውን ምርቶች እንዲያሳውቁ የተላከልንን ዝርዝር አያይዘን ደብዳቤ ልከናል ብለዋል፡፡

ዕድሉ ገቢን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም ስላለው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይከናወናልም ነው ያሉት፡፡

የኢኮኖሚክስና ልማት መምህር፣ አማካሪ እንዲሁም የንግድና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተንታኝ ዶክተር ንጉሤ ስሜ፥ ከቻይና የተገኘው ተጨማሪ ዕድል የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ከማሳደግ በተጨማሪ የተቀዛቀዘውን የአጎዋ እንቅስቃሴ ለማካካስ ያግዛል ብለዋል፡፡

ዕድሉ በሁለቱ ሀገራት ያሉትን አምራቾችና ሸማቾች በማገናኘት እና ምርቶቹ የሚገቡት ከቀረጥ ነጻ በመሆኑ ቻይናውያን ሸማቾች በርካሽ እንዲሸምቱ በማስቻል ጠቀሜታ እንዳለው ነው የሚናገሩት፡፡

እንደ ወይዘሮ ቁምነገር ገለጻ፥ ኢትዮጵያ 1 ሺህ 644 የምርት ዓይነቶችን ወደ ቻይና ከቀረጥ ነጻ እንድታስገባ ፈቃድ ብታገኝም ሁሉም የምርት ዓይነቶች ይላካሉ ማለት አይደለም፤ለዚህም ሁሉም የምርት ዓይነቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመረቱ አለመቻላቸውን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

ዶክተር ንጉሤ ስሜ በበኩላቸው፥ ባለሃብቱ በደንብ መበረታታት እና አምራቹም መጠንከር አለበት፤ መንግሥትም ከፖሊሲ አንጻር እንዴት አድርገን መጠቀም እንችላለን የሚለውን ሊያስብበት ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቀደም ብላ በተወሰኑ የሸቀጥ ዓይነቶች እድሉ የተሰጣት ሲሆን፥ ሰሞኑን አዳዲስ የሸቀጥ ዓይነቶች ተጨምረውላታል።

የቻይና መንግሥት ከሰሞኑ ለቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒቢሳው፣ ሌሴቶ፣ ማላዊ፣ ሳኦቶሜ- ፕሪንሲፔ ፣ ታንዛኒያ፣ ዑጋንዳ፣ ዛንቢያ እንዲሁም ለአፍጋኒስታን ከቀረጥ ነጻ ዕድል መስጠቱም ይታወቃል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.