Fana: At a Speed of Life!

በበጀት ዓመቱ ከቡና 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮ በጀት ዓመት 360 ሺህ ቶን ቡና በመላክ እስከ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ ሻፊ ዑመር ባለፉት አምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከ109 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት እንደቀረበ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የቡና ምርት 615 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረው ፥ ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ100 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለውም ነው ያነሱት፡፡

ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቤልጂየም፣ አውስትራሊያና ጃፓን የቡና ምርቱ ከተላከባቸው ሀገራት ይጠቀሳሉ።

የገበያ መዳረሻዎቹን በማስፋት ዘንድሮ ወደ ቻይና እና ኢንዶኔዥያ ቡና የመላክ ሥራ መጀመሩንና ይህም ለገቢው መጨመር ጉልህ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት 360 ሺህ ቶን ቡና በመላክ እስከ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ባለፈው ዓመት 302 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ኢዜአ አስታውሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.