ደቡብ ሱዳን ኢትዮ ቴሌኮም በዘርፉ ለሚያደርገው ተሳትፎ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ የተመራ የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አመራር ልዑክ በደቡብ ሱዳን የስራ ጉብኝት አድርጓል፡፡
ልዑካኑ ከደቡብ ሱዳን ኢንፎርሜሽን፣ ኮሙዩኒኬሽን እና የፖስታ አገልግሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ከብሄራዊ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን እና ከሌሎች የደቡብ ሱዳን ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ መሪዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይታቸውም በደቡብ ሱዳን ያለውን የቴሌኮም መሰረተ ልማት ፍላጎት እንዲሁም በሁለቱ እህትማማች ሀገሮች በትብብር ሊከናወኑ ስለሚችሉ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ዙሪያ መክረዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ሱዳን ያለውን የቴሌኮም ገበያ ለመቃኘት ያለውን ፍላጎት በማድነቅ ኢትዮ ቴሌኮም በዘርፉ ለሚያደርገው ተሳትፎ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ በበኩላቸው÷ ተቋሙ የ128 ዓመታት አንጋፋ እና ከአፍሪካ ቀዳሚ የቴሌኮም ኦፕሬተር መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ኩባንያው በኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማት ግንባታ እና አስተዳደር እንዲሁ የዋጋ ተመጣጣኝነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን መልካም ተሞክሮ በማጋራት የደቡብ ሱዳን መንግስት የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነት እና የዋጋ ተመጣጣኝነትን ለማረጋገጥ በሚያደረገው ጥረት ውስጥ አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ ለመሳተፍ ዝግጁነቱን አረጋግጠዋል።
በጉብኘቱም ወቅት ልዑካን ቡድኑ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሃላፊዎች ጋር በደቡብ ሱዳን ባላቸው የቢዝነስ እንቅስቃሴ እና ተሞክሮ ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኢንተርናሽናል ኢንተርኔት መገናኛ መስመር፣ በቴሌኮም መሠረተ ልማት ግንባታ እና የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅርቦት እና በሌሎች ተያያዥነት ባላቸው አገልግሎቶች ዙሪያ ከቴሌ ሞባይል ደቡብ ሱዳን ሃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ጋር የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ልዑካን ቡድኑ በነበረው ቆይታ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች እንዲሁም ከቴሌ ሞባይል ኩባንያ አመራር ለተደረገለት አቀባበል እና መስተንግዶ ልባዊ ምስጋናውን ማቅረቡን ከኢቲዮ ቴሌኮም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡