Fana: At a Speed of Life!

ወጋገን ባንክ ሽረ ከተማን ጨምሮ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ 12 ቅርንጫፎቹ ዳግም አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ግጭት ሥራ ካቆሙ 113 ቅርንጫፎች መካከል እስካሁን ድረስ 12 ወደ ሥራ ተመልሰው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ወጋገን ባንክ አስታውቋል፡፡

በባንኩ የሃብት ማሰባሰብና ቅርንጫፍ ባንኪንግ ዳይሬክተር መንግሥቱ ታደሰ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ግጭት ምክንያት 113 ቅርንጫፎች በተለያየ ጊዜ የአገልግሎት መቆራረጥ ደርሶባቸዋል፡፡

ይሁን እንጅ ባንኩ ያቋቋማቸው ኮሚቴዎች ባከናወኑት ሥራ ከሰላም ስምምነቱ በፊት አራት ቅርንጫፎቹ ወደ ሥራ ተመልሰው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ደግሞ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በራያ ጥሙጋ እና አላማጣ ከተማ እንዲሁም ከትናንት ጀምሮ ደግሞ በሽረ ከተማ የሚገኙ ሥድስት ቅርንጫፎች ዳግም ወደ አገልግሎት መመለሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ባንኩ በሽረ ዲስትሪክት ስር በሚገኙት ሽረ፣ እንዳሥላሴ፣ ምድረ ገነት፣ ዕዳጋ ሽረ፣ ስሁል ሽረ እና ምድረ ሓየሎም ቅርንጫፎቹ ነው ዳግም በትናንትናው ዕለት አገልግሎት መስጠት የጀመረው።

ዳግም ሥራ በጀመሩ ቅርንጫፎችም መሠረታዊ የሚባሉ የባንክ አገልግሎቶች ማለትም÷ ገንዘብ መቀበል፣ ገንዘብ መክፈል፣ ገንዘብ ማስተላለፍ እና የውጭ ሀገር ሃዋላን ለደንበኞች ማድረስ (የሀዋላ አገልግሎት) እየተሠጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አገልግሎቱ ዳግም በተጀመረባቸው ቅርንጫፎች የብሔራዊ ባንክ አሠራርን በተከተለ ሁኔታ ደንበኞች ከዚህ ቀደም እንደነበረው መታወቂያ እና የባንክ ደብተር በማቅረብ ያለምንም ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በአክሱም እና ዐድዋ ከተሞች ደግሞ በቅርቡ አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታኅሣሥ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በሽረ፣ አላማጣ እና ኮረም እንዲሁም አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ ታኅሣሥ 11 ቀን 2015 ዓ.ም በሽረ እንዳ ሥላሴ እና አካባቢው ዳግም አገልግሎት እንደጀመሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.