የሀገር ውስጥ ዜና

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ዘጠነኛ አመት በመገናኛ ብዙሃን ታስቦ ይውላል

By Tibebu Kebede

April 01, 2020

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ዘጠነኛ አመት በመገናኛ ብዙሃን ታስቦ እንዲውል ተወሰነ።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ በወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በስፍራው የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 9ኛ አመት እንደማይከበር አስታውቋል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ ከምንጊዜውም በላይ በሃገራዊ አንድነት ስሜት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በግድቡ ግንባታ ላይ ለተሰማሩ ሰራተኞች ተገቢው የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ግንባታው በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ግንባታው በሁለት ፈረቃ እየተከናወነ እንደሚገኝና አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 72 ነጥብ 4 በመቶ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የግድቡ ግንባታ የተበጀተለት በጀት እና ትኩረት እንደማይቀንስም አስረድተዋል።

ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሃገራት እና ከሌሎች ሃገራት ጋር የምታደርገውን የዲፕሎማሲ ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አውስተዋል።

በሚቀጥሉት 100 ተከታታይ ቀናት በሚሰራው የኮንክሪት ሙሌት ስራም በዚህ አመት ማብቂያ ላይ የውሃ ሙሌት ስራው እንደሚጀመርም ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ ለግድቡ የሚደረገው ህዝባዊ ትሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በምስክር ስናፍቅ