Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ እያደረገባቸው ያሉት ቀሪ 23 መዳረሻዎች የቫይረሱ ስርጭት ያልበዛባቸው ወይንም ስርጭቱን የተቆጣጠሩ ሀገራት መሆናችውን ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ወደ 87 የበረራ መዳረሻዎች የሚያደርጋችውን በረራዎች ያቋረጠ ሲሆን፣ በመቀጠልም ወደ ተቀሩት 23 መዳረሻዎች የሚያደርጋችውን በረራዎች በየቀኑ እየቀነሰ መሆኑን ገለፀ።

ሰሞኑን ከዚህ እና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ሚዲያ ሀሰት እና ከእውነት የራቀ መረጃ እየወጣ መሆኑን ዓየር መንገዱ ገልጿል።

በመግለጫው በረራ ካቆምንባቸው 87 ሀገራት መካከል ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋባቸው ሀገራት ጣሊያን እና ስፔን እንዲሁም በርከት ያሉ የአውሮፓ ሀገራት ይገኙበታል ብሏል።

ይህም ያተረገው ከቫይረሱ ስርጭት ጋር የተያያዘ ጥንቃቄን ለማድረግ በማሰብ ነው ያሉት ዓየር መንገዱ፥  እስከ አሁን ድረስ የምንበርባቸው መዳረሻዎች (23 መዳረሻዎች) የቫይረሱ ስርጭት ያልበዛባቸው ወይንም ስርጭቱን የተቆጣጠሩ ሀገራት መሆናችውን ገልጿል።

ነገር ግን አየር መንገዱ የኮሮናን ቫይረስ (ኮቪድ 19) ለመከላከል የሚረዱ ህይወት አድን የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ሀገራት በማጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ይህም የበረራ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በጭነት ማመላለሻ አውሮፕላኖቻችን እንዳደረገና ለዚህም የሰውን ህይወት ለማትረፍ ለሚያከናውናቸው ስራዎች ከተለያዩ ሀገራት፣ ተቋማት እና መንግስታት ምስጋና እና አድናቆትን እያገኘ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞቹ፣ የመንገደኞቹ፣ የአጋር ድርጅቶች ሰራተኞች እና የስራ ባልደረቦች እንዲሁም በአጠቃላይ የህብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ የሚወስዳቸውን የመከላከል ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለፀው።

በተጨማሪም ወደ ሀገሮቻቸው ተመላሽ የሆኑ መንገደኞችን ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ፣ ወደ አሜሪካ እና ካናዳ እያጓጓዘ እንደሆነና በርካታ ኢትዮጵያውያንንም ወደ ሀገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ማድረጉን አመልክቷል።

በቀጣይም የኮሮናን ቫይረስ (ኮቪድ 19) መከላከያ የህክምና ቁሳቁሶችን ወደተለያዩ የሃገራችን ክልሎች ማድረሱን እንደሚቀጥል በመግለጫው አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.