Fana: At a Speed of Life!

በሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የሚፈጸሙ የሥነ ምግባር ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አሳሰበ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተቋቋመበት መርህና አላማ በተቃረነ አኳኋን በተለያዩ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የሚፈጸሙ ህጋዊና ሙያዊ የሥነ ምግባር ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አሳሰበ።

ባለስልጣኑ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ለኢትዮጵያውያን መልካም ዕሴቶች መጎልበት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው መንግስት እንደሚያምን ገልጿል።

መንግስት የመገናኛ ብዙኃኑ ያላቸውን አወንታዊ ሚና በማመን ለተቋማቱ ህጋዊ እውቅና በመስጠት ድጋፍና እገዛ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የገለጸው።

የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሃይማኖታዊ አስተምህሯቸውን ለተከታዮቻቸው ሲያስተምሩ የሌሎችን ሃይማኖትና እምነት አክብረው እንዲያስተምሩ፣ ከተቋቋሙበት ሃይማኖታዊ ጉዳይ ውጭ ሌሎች ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች እንዳያስተላልፉ እና ከጥላቻ፣ በዜጎች መካከል አብሮ መሆንን ከሚያውክ በማንኛውም አግባብ ሁከትና ግጭት ሊቀሰቅስ ከሚችል በዜጎች ላይ ሥነ ልቦናዊም ሆነ አካላዊ ጥቃት እንዲደርስ ከሚያነሳሳ ንግግር እና ከመሰል አሉታዊ መልዕክቶች እንዲታቀቡ ይጠበቅባቸዋልም ብሏል።

በተጨማሪም ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራም ሲያሰራጩ በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳት፣ የሌሎችን ሃይማኖት ማንኳሰስ እንዲሁም በሃይማኖቶች ተከታዮች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀስቀስም የተከለከለ መሆኑንም ነው የገለጸው።

ይሁን እንጅ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ክትትል ክፍል ግኝቶች፣ ከዜጎች እና ከተቋማት የደረሱ ቅሬታዎችና ጥቆማዎች የተወሰኑ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ከጊዜ ወደጊዜ ከሚጠበቅባቸው ህጋዊ፣ ማህበራዊና ሙያዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ መልዕክቶች እንደሚተላለፉባቸው መስተዋሉን አንስቷል።

አልፎም የዜጎችን የመቻቻል እና አብሮ የመኖር እሴት የሚሸርሽሩ ሁከትና ግጭት የሚጋብዙ እንዲሁም በግለሰብና ማህበረሰብ ላይ አካላዊ ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሱ ንግግሮች መሰራጨታቸውንም ነው የጠቀሰው።

ከዚህ አንጻርም በመገናኛ ብዙኃን ተሰራጭተው የዜጎችን ሰላምና አብሮነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እና ሃላፊነት የጎደላቸው መልዕክቶችን በሚያስተላልፉ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያስታወቀው።

ባለስልጣኑ ከሰሞኑ በተወሰኑ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ላይ የቀረቡለትን ቅሬታዎች ከህግና ከሙያ ሥነ ምግባር አንጻር መርምሮ እንደ አስፈላጊነቱ ውጤቱን ለፍትህ አካላት እንደሚያቀርብም አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.