Fana: At a Speed of Life!

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት ዋናው ተግባር ለችግሩ መነሻ መፍትሔ መስጠት ነው -አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት ዋናው ተግባር ለችግሩ መነሻ መፍትሔ መስጠት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

በተጠናከረ የማሕበረሰብ ተሳትፎ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ እንከላከል በሚል ርዕስ በሆሳዕና ከተማ ማህበረሰቡን ያሳተፈ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሀገሪቱን ከገጠሟት ፈተናዎች ዋነኛ ከሆነው ከሰሜኑ ጦርነት ባሻገር ሌላ ፈተና የሆነው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ነው ብለዋል፡፡

መድረኩ በሆሳዕና የተካሔደበት ዋናው ምክንያት ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት በሀገራችን ከፍተኛ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ካለባቸው አካባቢዎች በዋነኝነት የሚጠቀስ በመሆኑ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይም ችግሩ ጎልቶ ወደ ሚታይባቸው ወደ ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የሕዝብ ንቅናቄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ደመቀ አመላክተዋል፡፡

የጥቂቶችን ስኬት በማየት ብዙዎች በሚያሳዝን፣ ሰብዕናን በሚፈትን ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደተመለሱ እና በተጨማሪም ከ5 ሺህ በላይ እስረኞች በታንዛኒያ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን አስከፊነት ገልጸው ለዚህም ዋናው መፍትሔ ምንጩን ማድረቅ ነው ብለዋል።

በምንተስኖት ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.