Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የብዝሃ ቋንቋ ስርዓተ ትምህርት ለመተግበር እየተደረገ ላለው የዳሰሳ ጥናት የግብዓት ማሰባሰቢያ የምሁራን መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች የብዝሀ ቋንቋ ስርዓተ ትምህርት ለመተግበር የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ውጤት ግብዓት ማሰባሰቢያ የምሁራን መድረክ እየተካሄደ ነው።

የብዝሃ ቋንቋ ስርዓተ ትምህርት ለመተግበር የተካሄደውን የዳሰሳ ጥናት በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ከሀምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሂድ መቆየቱ ተነግሯል።

ጥናቱ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ አንድ የሀገር ውስጥና አንድ የውጪ ቋንቋ ለማካተት የተደረገ ጥናት መሆኑን የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነ መስቀል ጠና ተናግረዋል።

በ2014 ግንቦት ወር ላይ የተጀመረው ጥናቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሀሳቦች በግብአትነት የወሰደ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለትም ከምሁራን ሀሳቦችን ለማሰባሰብ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

ቋንቋ ለማህበራዊ ብቻም ሳይሆን ለኢኮኖሚውም ወሳኝ በመሆኑ፥ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ የሚካተቱት ቋንቋዎች በሚገባ ታስቦባቸው የሚተገበሩ ናቸው ሲሉም ዶክተር ብርሀነ መስቀል ጠና ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፥ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አሳታፊ በሆነ መልኩ የብዝሃ ቋንቋ ስርዓተ ትምህርት ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን አንስተዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የተገኘው ግብዓት ለሌሎች አካባቢዎችም ምሳሌ ይሆናል ብለዋል።

ህጻናትን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር የፖሊሲው እቅድ ነው፤ ነገር ግን አተገባበሩ ውይይት ያስፈልገዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ምሁራኑም በእውቀት ላይ የተመሰረተ እና ከስሜት የፀዳ አስተያየት በመስጠት ለግብዓት ማሰባሰቡ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.