እንግሊዝ ከ46 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የግል የመከላከያ መሳሪያዎች ድጋፍ ለኢትዮጵያ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዝ ኢምባሲ በአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት በኩል ከ46 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የግል የመከላከያ መሳሪያዎች ድጋፍ ለኢትዮጵያ አደረገ፡፡
ድጋፎቹ የኢንፌክሽን መከላከያ እና የኮቪድ 19 መቆጣጠሪያ የሚውሉ ቁሳቁሶችና ግብአቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ታስቦ የተለገሱ እነደሆኑም ነው የተነሳው፡፡
ድጋፉም በአለም አቀፍ የስደተኛ ድርጅት በኩል ከፎርዬን ኮመን ዌልዝ ኤንድ ድቭሎፕመንት ኦፊስ እንደተለገሰ ተጠቁሟል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በድጋፍ ርክክብ ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት ፥ የጤና ሚኒስቴር ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ፣ በተለያዩ የጤና ዘርፎች ላይ በአጋርነት ለበርካታ ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ድጋፉ ለኮቪድ 19 መከላከልና ለጤናው ስርአት መጠናከር ትልቅ አስተዋጾኦ እንደሚኖረው ገልጸው ፥ በሽታውን ለመግታት የእንግሊዝ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያልም ነው ያሉት፡፡
እየተደረገ ላለው ድጋፍ የእንግሊዝ መንግስት እና የአለም አቀፍ የስደተኛ ድርጅትን አመስግነው ፥ ድጋፉና በአብሮነት መስራቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የእንግሊዝ ኢምባሲ በኢትዮጵያ የሪዚሊያንስ ኤንድ ሂማኒቴሪያን ቲም ሊደር የሆኑት ሚስ ጄንፌር ስቶኪል በበኩላቸው ፥ የእንግሊዝ መንግስት 846 ሺህ የግል መከላከያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
መሳሪያዎቹ የጤና ባለሙያዎች ስራቸውን ሲሰሩ ራሳቸውን እንዲከላከሉ ይረዳሉም ነው ያሉት፡፡
የአለም አቀፍ የስደተኛ ድርጅት በኢትዮጵያ ቺፍ ሚሺን ኦፊሰር የሆኑት ሚስተር ጂያን ዦሃኦ አለም አቀፍ የስደተኛ ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበትና በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ድጋፎቹን ሚኒስትሯ ከሚስ ጄንፌር ስቶኪል እና ሚስተር ጂያን ዦሃኦ እጅ መረከባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡