Fana: At a Speed of Life!

ጦርነቱ እድሜ እና ሕልማችንን የሰረቀ ነው- የትግራይ ወጣቶች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ወጣቶች ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ ህልማቸውን ያደበዘዘ እንደሆነ ወጣቶቹ ተናግረዋል።

የሽረ ከተማ ነዋሪዎቹ ወጣት ክብሮም ግዑሽና ተስፋ ገብረ ጊዮርጊስ ጦርነቱ በርካታ ሺህ ወጣቶችን መቅጠፉን፣ እቅድና ተስፋቸውን ማሰናከሉን አብራርተዋል።

ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በጂኦሎጂ ተመርቆ በጃፓን ካምፓኒ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረው ክብሮም በሚያገኘው ገቢ ‘‘ቤተሰቤን አስተዳድር’’ ነበር ይላል።

በጃፓን ሀገር ተጨማሪ ስልጠና ለመውሰድ የሚያስችለውን እድል አግኝቶ በዝግጅት ላይ ሳለም ጦርነቱ በመከሰቱ ጉዞውም ስራውም መስተጓጎል ገጠመው።

በተማረበት ስራ የተሻለ ገቢ ያገኝ የነበረው ክብሮም ‘‘እድለኛ ሆኜ ተረፍኩ እንጂ ጦርነቱ በርካታ እኩዮቼን የቀጠፈ ነው’’ ሲል ይናገራል፡፡

ይሄ ጦርነት እኔን ከረጂነት ወደ እርዳታ ጠባቂነት ቀይሮኛል የሚለው ክብሮም ፥ ብዙ እቅዶቹም እንደተሰናከሉ ነው ያከለው።

በተመሳሳይ በጅማ ከተማ ትዳር መስርቶ የአንድ ልጅ አባት የሆነው ተስፋም ፥ የራሱን ስራ በመስራት ይተዳደር ነበር ፤ ከዚህ በተጨማሪም በፋሽንና ዲዛይን ስራ የበለጠ ስኬትን አቅዶ ይታትር ነበር።

ከጅማ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ሽረ በመጣበት አጋጣሚ ድንገት የጀመረው ጦርነት ከልጁም፣ ከስራውም፣ ከኑሮውም ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቆራርጦ እንዲቆይ እንዳደረገው ይጠቅሳል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት እኒህ ወጣቶቹ ጦርነቱ የትግራይ ህፃናትና ወጣቶችን እድሜና ህልም የበላ ነው ይሉታል።

ህፃናት በኮሮና ምክንያት ወደተቋረጠ ትምህርታቸው አለመመለሳቸውን በማከል ይህም የመማሪያ ጊዜያቸው እንዲተላለፍ አድርጓልም ነው ያሉት።

ጦርነት ፍፁም ሊደገም የማይገባው፣ የትግራይ ህዝብም የሰለቸውና የበቃው እንደሆነም አበክረው ይናገራሉ።

የሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግም ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት ወጣቶቹ ይጠይቃሉ፡፡

በአፈወርቅ እያዩና ለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.