Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶች እየተመለሱ በመሆኑ ወደ መደበኛ ህይወታችን የመመለስ ተስፋ አሳድሮብናል – ነዋሪዎች

 

አዲሰ አበባ፣ ታኅሣሥ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መሰረታዊ አገልግሎቶች እየተመለሱ በመሆናቸው ወደ መደበኛ ህይወታቸው የመመለስ ተስፋ እንዳሳደረባቸው በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅኝት ባደረገባቸው ሽራሮ፣ ኣዲ ሀገራይ፣ ኣዲ ዳዕሮና ሽረ ከተሞች አገልግሎቶችን ለመመለስ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ነዋሪዎቹ ከጊዜያት በኋላ የተገኘው አንፃራዊ ሰላም መሰረተ ልማቶችን እንዲያገኙ ምክንያት እንደሆናቸው አንስተው ፥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በከተሞቹ የቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሀ፣ የባንክ፣ የጤና እና መሰል አገልግሎቶች እየተመለሱ መሆናቸውን መመልከት ችለናል።

ከፌዴራል መንግስት የተላከው የባለሙያዎች ቡድን አገልግሎቶችን ለመመለስ የሚያደረገውን ጥረትንም ተመልክተናል።

ጣቢያችን የሽራሮ ጤና ጣቢያ እና የስሁል ሆስፒታልን ላይ ባደረገው ምልከታ ፥ በጤና ተቋማቱ መደበኛ አገልግሎቶች ተጀምረዋል።

በተቋማቱ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ጦርነቱ ባስከተለው ተፅዕኖ አገልግሎቶች ተቋርጠው እንደነበር ባለሙያዎችም ጦርነቱን ሽሽት ተሰደው እንደቆዩ ነግረውናል።

እየተሻሻለ የሚገኘውን የሰላም ሁኔታ ተከትሎ ወደ ስራቸው መመለሳቸውን፣ የመድሀኒት አቅርቦትም እየተሻሻለ መሆኑን፣ በጤና ሚኒስቴር የሚደረገው ድጋፍ እንዳበረታቸውም ነው የተናገሩት።

በጤና ተቋማት ሲታከሙ ያገኘናቸው ነዋሪዎች በህክምና እጦት በርካታ ዜጎች መጎዳታቸውን፣ በስኳርና መሰል የባለሙያ ክትትል በሚፈልጉ በሽታዎች ተቋርጦ የነበረው አገልግሎትም እፎይታ እንደሰጣቸው አክለዋል።

ነዋሪዎቹ ጦርነቱን ሽሽት ከአካባቢዎች ርቀው ሄደው የነበሩ ሲሆን ፥ የሰላም ሁኔታው መሻሻሉን ተከትሎ ወደ ከተሞች እየተመለሱ ነው።

በአፈወርቅ እያዩና ለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.