Fana: At a Speed of Life!

ወደ ሽረ ከተማ ነዳጅ እየተጓጓዘ ነው – የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ሽረ ከተማ ነዳጅ እየተጓጓዘ መሆኑን የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በባለስልጣኑ የነዳጅ አቅርቦት፣ ሎጅስቲክስና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ሹመት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ጥገናቸው ለተጠናቀቁ እና ምርቱን ለጠየቁ የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ ለማቅረብ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

በዚህም በሦስት ሚኒስትር ዴኤታዎች የተመራ ቡድን በጎንደር-ደባርቅ-ሊማሊሞ-ማይጠምሪ- ሽረ እንዲሁም በደሴ- ወልዲያ- ሀራ መገንጠያ- ቆቦ- አላማጣ- ኮረም እና በዓብዓላ መስመር የነዳጅ ማደያዎችን ሁኔታና ነዳጅ ለማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምልከታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከቡድኖቹ ምልከታ በኋላ ከማደያዎቹ ባለቤቶች ጋር ማደያዎቹ በአስቸኳይ በሚጠገኑበት ሁኔታ ላይ በተደረገው ተከታታይ ውይይት የተወሰኑት መጠገናቸውን እና በጥገና ሂደት ላይ ያሉ መኖራቸውንም ነው የተናገሩት።

በዚህም በሽረ ከተማ ለሚገኝ አንድ ማደያ ነዳጅ እየተጓጓዘ ሲሆን፥ በዚሁ ከተማ ለሚገኙ ተጨማሪ አንድ ማደያ እና በማይጠምሪ ለሚገኝ አንድ ማደያ ደግሞ በዚህ ሣምንት ነዳጅ ማጓጓዝ እንደሚጀመርም አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በደሴ-ወልዲያ- ሐራ መገንጠያ- ቆቦ መስር ላሉ ማደያዎች ግን ነዳጅ እቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአላማጣ እና ኮረም የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ባለቤቶች የገንዘብ እጥረት ስላለብን ነዳጅ ለማዘዝ አንችልም በማለታቸው ነዳጅ ለማቅረብ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡ ባለቤቶቹ በሚጠይቁ ጊዜ ምርቱ እንደሚቀርብም ነው የተመላከተው፡፡

በዓብዓላ ያሉ ሁለት ማደያዎች ባለቤቶቻቸው ባለመገኘታቸው ነዳጅ ለማቅረብ የሚያስችል ሁኔታ ቢኖርም ሁኔታው መስተጓጎሉን አንስተዋል፡፡

ለጊዜው ግን ባለስልጣኑ ከአፋር ክልል ንግድ ቢሮ ጋር በመነጋገር በጀሪካን እና በበርሜል ነዳጅና ቤንዚል እየቀረበ መሆኑን ተናግረው ባለቤቶች ተገኝተው ለኩባንያዎቹ ክፍያ ሲፈጽሙና ነዳጅ እንዲቀርብላቸው ጠይቀው አስፈላጊውን ሂደት እንደጨረሱ ነዳጁን ለማቅረብ እንደሚቻልም አረጋግጠዋል።

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.