ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የሆነ በህገ-ወጥ መንገድ የተሰበሰበ የውጭ ምንዛሪ ታገደ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የሆነ በህገ-ወጥ መንገድ የተሰበሰበ የውጭ ምንዛሪ መታገዱን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
መንግስት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ባንኮች በውጭ ሀገራት ገንዘብ የሒሳብ ደብተር የሚከፍቱበትን የዳያስፖራ አካውንት ህግና የአሠራር ስርዓት በመጣስ የተለያዩ ግለሰቦች በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን አገልግሎቱ ባካሄደው ክትትል ማረጋገጥ መቻሉ ተገልጿል፡፡
በዚሁ መሠረት አገልግሎቱ እስካሁን ባደረገው ክትትል፣ የትንተናና ማጣራት ስራዎች 85 ግለሰቦች የተሳተፉበት እና መጠኑ 20 ሚሊየን 226 ሺህ 583 ዶላር የውጭ ሀገር ገንዘብ በባንክ እንዲታገድ በማድረግ ለወንጀል ምርመራ መተላለፉ ነው የተመላከተው፡፡
ወንጀሉ የተፈፀመው የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችንና የማጭበርበር ስልቶችን በመጠቀም ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል አንደኛ ውጭ ሀገር ሳይሄዱ ውጭ ሀገር ሄደው የተመለሱ በማስመሰል ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በማቅረብና በመጠቀም እና ሁለተኛ ከውጭ አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው በመግባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው እንደገቡ በማስመሰል ቀሪውን በህገ-ወጥ መንገድ ከጥቁር ገበያ ላይ በመሰብሰብና ሀሰተኛ ሰነድ/ዲክላራሲዮን በማቅረብ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ሶስተኛ የሌላውን ሰው ዲክላራሲዮን የራስ አስመስለው በመጠቀም እንዲሁም አራተኛ ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በተለያዩ ባንኮች የዲያስፖራ አካውንት በመክፈትና በመጠቀም በአጠቃላይ ሌሎች ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በመጠቀም የወንጀል ተግባራት መፈጸማቸው ተጠቁሟል፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባካሄደው ክትትል፣ ትንተናና ማጣራት ሂደት ውስጥ ግለሰቦቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዳያስፖራ አካውንትን በሚመለከት ያወጣውን መመሪያ፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 እንዲሁም የወንጀል ህግን በመተላለፍ የተፈጠረውን ዕድል ለወንጀል መጠቀሚያ ማዋላቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
በመሆኑም በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊዎች ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጉዳዩ ለወንጀል ምርመራ የተላለፈ ሲሆን፥ አገልግሎቱ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ በመሰል የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካላት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ተገንዝበው ከድርጊቱ እንዲታቀቡም አገልግሎቱ በጥብቅ አሳስቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television