Fana: At a Speed of Life!

በሙስና ላይ የተጀመረውን የተቀናጀ ትግል አጠናክሮ በማስቀጠል ከግብ ለማድረስ ይሰራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች የተቀራረበ ፖለቲካዊ ግንዛቤ በመፍጠር አንድነቱን አጠናክሮ የህዝቡን ችግር እንዲቀርፍ ለማስቻል ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ  አዳነች አቤቤ በማጠቃለያ መድረኩ ላይ እንደተናገሩት÷ ብሄራዊ አንድነትን ያከበረ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት የመገንባት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግቦችን ለማሳካት የተጀማመሩ መልካም ስራዎችን ለማጠናከር ስልጠናው የራሱ ድርሻ አለው።

ማንነቶችን ለግል ፍላጎቶች ማሳኪያ ለማዋል የሚደረጉ ከህዝብ እሴት ያፈነገጡ ፅንፍ የረገጡ አካሄዶች ለፖለቲካ ሸቀጥነት እንጂ ማንንም እንደማይወክሉ አንስተዋል፡፡

ስለሆነም እራስን አፅድቶ ከስር ከስር እያረሙ መጓዝና ህዝቡን በማሳተፍ በሌብነት ላይ የተጀመረው የተቀናጀ ትግል አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ  ነው ከንቲባዋ ያስገነዘቡት፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በተለይም የአሁኑ አመራር የፀረ ሌብነት ትግል አጀንዳ በማድረግ ሲታገልበት የቆየ መሆኑን ጠቁመው÷ አሁንም አመራሩ መላውን ህዝብ በማሳተፍ የተጀመረውን ትግል ከግብ ለማድረስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው÷ አመራሩ ከፅንፈኝነትና ከአክራሪነት የሚጠቀምም የሚያተርፍም እንደሌለ በመገንዘብ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ሊተረጉመው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ብልፅግና በሌብነት ላይ ቀይ መስመር አስምሮ በመነሳቱ በሌብነት ተግባር የተሳተፉና የተሰማሩ ግለሰቦችን በህግ አግባብ ተጠያቂ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የአሰራር ግልፀኝነትን በመፍጠር የሌብነት ምንጮችን የማድረቅ ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ÷ አመራሩ በመርህ ላይ በመቆም ፅንፈኝነትን፣ ሌብነትን እንዲሁም አክራሪነትን በመታገል ህዝቡ የጣለበትን ኃላፊነት መወጣትና ሰላሙን አስተማማኝ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.