Fana: At a Speed of Life!

በብዝሀ ቋንቋ ዙርያ በተጠና የጥናት ውጤት ላይ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በብዝሀ ቋንቋ ዙርያ በተጠና የጥናት ውጤት ላይ ውይይት አደረጉ፡፡

ውይይቱ ለብዝሀ ቋንቋ አተገባበር ከአፍ መፍቻ በተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጪ ቋንቋዎችን በስርዓተ ትምህርት ለማካተት በተደረገ የጥናት ውጤት ላይ ነው የተደረገው።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷ ጥናቱ ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ሲደረግ መቆየቱንና በውይይት እየዳበረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ ጥናቱን የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተወያይተውበት በቀጣይ ህዝቡን ማወያየት እንደሚያስፈልግ ማስረዳታቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የጥናት ፅሁፉን ያቀረቡት የኮተቤ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶ/ር ዮሴፍ ፥ ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን ማወቅ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ማህበራዊ መስተጋብርንና ትስስርን እንደሚያጠናክርም ነው ያነሱት፡፡

አክለውም ሌሎች ፍልስፍናዊና ባህላዊ እውቀቶችን እንደሚያጎናፅፍ እንዲሁም በሀገሪቱ በተለይም ኦሮሚያ ክልል ከሌሎች ክልሎች ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎችና በሌሎችም ክልሎች የተጀማመሩ ስራዎች ያስገኟቸውን መልካም ውጤቶች ጠቅሰዋል።

በተደረገው ጥናት ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎችና ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ከቅርበት ከተደራሽነትና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምክንያቶች ሌሎች የአካባቢው ቋንቋዎችንም ለመማር ምርጫቸው መሆኑ መረጋገጡ ቀርቧል።

በውይይቱ የተሳተፉ አመራሮችም የቀጣዩ ትውልድ ማህበራዊ ትስስር የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብዝሀ ቋንቋ አተገባበር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.