የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የተለያዩ የቤት አማራጮችን መተግበር ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች የዜጎችን የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎት ለማጣጣም በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የተለያዩ የቤት አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር በቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ልማት የተዘጋጀ ስልጠና ከክልል ከተሞች ለተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሰጠ ነው፡፡
በወቅቱ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሔለን ደበበ እንደተናገሩት ፥ በከተሞች የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ተሳታፊነት የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ ሚኒስቴሩ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ እየሠራ ነው፡፡
መንግስት እያካሄደው ከሚገኘው የቤት ግንባታ ባሻገር 80 በመቶ የሚሆነውን የግሉ ዘርፍ ሁሉንም ዜጎች ማእከል ያደረገ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ያለውን ማህበረሰብ የቤት ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አቅምን በሁሉም ከተሞች በመገንባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡