Fana: At a Speed of Life!

ሞሮኮ በቻን ውድድር ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጠች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 19 ፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።

ብሄራዊ ቡድኑ ከሞሮኮ አልጄሪያ የቀጥታ በረራ ካልተፈቀደለት በአልጀሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የቻን ውድድር ሊሳተፍ እንደማይችል አስታውቋል።

ቅድመ ሁኔታውን ያስቀመጠው የቻን አስተናጋጇ ሀገር አልጀሪያ ከሞሮኮ ጋር ባላት የፖለቲካ አለመግባባት በሞሮኮ የተመዘገቡ የመንገደኞች እና የጦር አውሮፕላኖች በአየር ክልሏ እንዳያልፉ መከልከሏን  ተከትሎ ነው፡፡

አልጀሪያ ባስቀመጠቸው ህግ መሰረት የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ከዋና ከተማዋ ራባት ውድድሩ ወደ ሚደረግባት የአልጀሪያዋ ኮንስታንተይን ከተማ የቀጥታ በረራ ማድረግ አይችልም፡፡

በመሆኑም የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን የቀጥታ በረራ ካልተፈቀደለት በቻን ውድድር ሊሳተፍ እንደማይችል የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያስታወቀ ሲሆን ይህ ውሳኔም ለውድድሩ ድምቀት ስጋት ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡

በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የቻን የአፍሪካ ሀገራት ውድድር ከቀናት በኋላ በአልጄሪያ የሚከናወን ሲሆን 18 ሀገራት እንደሚሳተፉ የሀገሪቱ የዜና አውታር ዘገባ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.