Fana: At a Speed of Life!

መገናኛ ብዙኀን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል – በሽረ ከተማ የሕዝብ መድረክ ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መገናኛ ብዙኀን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንዲሰሩ በሽረ ከተማ በተካሔደው የሕዝብ መድረክ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎቸ ገለጹ፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች÷ የተፈናቀሉት እንዲመለሱ፣ የሰብዓዊ ድጋፉ እንዲጠናከር፣ መገናኛ ብዙኀን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ፣ ትምህርት ቤቶች እና የትራንስፖርት አማራጮች በፍጥነት እንዲከፈቱ ጠይቀዋል፡፡

“የትግራይ ምድር የጥይት ድምፅ ሳይሆን የልማት ዜናን ይናፍቃል” ያሉት ተሳታፊዎቹ÷ “ከዚህ በኋላ ችግሮች በጦርነት ሜዳ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ሊፈቱ ይገባል” ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የሐይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው ተሳታፊዎች የተናገሩት፡፡

“ለዜጎች ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ሁሉ” የተጀመረውን ሰላም በማስቀጠል ከሕዝብ ጎን እንዲቆሙም ተሳፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስጀመር ሁኔታዎች እየተጠኑ መሆኑ እና ትምህርት ቤቶች ዳግም እንዲከፈቱ ድጋፍ እንደሚደረግም በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ፣ ለይኩን ዓለምና ታሪኩ ወልደሰንበት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.