የቁልቢ እና የሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግስ በሰላም ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓመታዊው የቁልቢ እና የሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግስ በሰላም መጠናቀቁን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ እና የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቁ፡፡
የሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ናስር መሀመድ እንደገለጹት፥ ዓመታዊው የንግስ በዓል በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና እንግዶች በተገኙበት በሰላም ተከብሮ ተጠናቋል።
የዘንድሮ ንግስ በዓል አንድም የወንጀል ድርጊት ያልተፈፀመበትና የትራፊክ አደጋ ያልተመዘገበበት ሆኖ እንደተጠናቀቀም ኮማንደር ናስር አረጋግጠዋል።
የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተስፋዬ ቱንጋሞ በበኩላቸው፥ በቂ ስራዎች አስቀድሞ መሠራታቸው የንግስ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አግዟል ብለዋል።
በዓሉን ለማክበር ከቀናት በፊት እንግዶች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን የገለፁት ኮሚሽነሩ በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ችግር ማክበር መቻሉንም ተናግረዋል።
በዕለቱ አንድ የእጅ ስልክ ንጥቂያ ወንጀል የተፈፀመ ሲሆን፥ ወንጀለኛውም በበዓል አከባበሩ ላይ በነበረው ጊዜያዊ ችሎት በ2 ዓመት ከ3 ወር እስራት ወደ ማረሚያ እንዲወርድ መደረጉን ነው የገለጹት።
ለታየው ፍፁም ሰላማዊ እንቅስቃሴ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ እና የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋና አቅርበዋል።
በመቅደስ አስፋው