Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ለገና በዓል መሰረታዊ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ ተገብቷል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለገና በዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱን የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
 
በኤጀንሲው የግብይትና መሰረተ ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ደብሪቱ ለአለም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ለመጪው የገና በዓል ለህብረተሰቡ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዝግጅት ተደርጓል፡፡
 
በዚህ መሰረት በ150 መሰረታዊ ሸማቶች እና በ11 ዩኒየኖች የተለያዩ ምርቶችን ከአምራች ህብረት ስራ ማህበራት እና ከኢንዱስትሪዎች የማስገባት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
 
ከምግብ ዘይት ጋር ተያይዞ በሸማች ማህበራት ከሚቀርቡት ሰን ፍላዎር እና ሌሎች ምርቶች በተጨማሪ በመንግስት ድጎማ አራት ፋብሪካዎች ለበዓሉ ከ2 ሚሊየን በላይ ሊትር ዘይት ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡
 
እንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦን በተመለከተም ኢትዮ አግሪ ሴፍት እና ሌሎች ዩኒየኖች በጉለሌ፣ ቤተል፣ የካ እና አቃቂ አካባቢ በሚገኙ የከብት ገበያዎች እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል፡፡
 
በከተማዋ የሚገኙ 225 ልኳንዳ ቤቶችም የበሬ ስጋ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ የሚያቀርቡ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
 
ስኳር ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት አማካኝነት በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
 
ዶሮን በተመለከተም የተበለተ እና በህይወት ያለ ዶሮ ለገበያ እንደሚቀርብ ጠቁመው÷ ለዚህም ከኤል ፎራ እና ሌሎች አቅራቢዎች ጋር ስምምነት መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡
 
ጤፍ ፣ ዱቄት፣ ጥሬ ስንዴ፣ ሽንኩርት እና ሌሎች ግብዓቶችም ከክልል አቅራቢዎች ጋር በመነጋገር በቂ የሆነ አቅርቦት ወደ መዲናዋ መግባት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
 
ሸማች ማህበራት የትራንስፖርት እና ሌሎች ወጪዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ከሚጨምሩት ከ50 ሳንቲንም እስከ 1 ብር ውጪ የተጋነነ ዋጋ መጨመር እንደማይችሉም አስገንዝበዋል፡፡
 
ነጋዴዎች እና አቅራቢዎች በዓሉን ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ዳይሬክተሯ አሳስበዋል፡፡
 
ማህበረሰቡም ለበዓሉ በቂ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት መኖሩን በመገንዘብ በከተማዋ ከቀረቡ አማራጮች ለአላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ሳይዳረግ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ጠይቀዋል፡፡
 
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.