Fana: At a Speed of Life!

ደረሰኝ ሳይዙ ሸቀጦችን ጭነው በሚንቀሳቀሱት ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ደረሰኝ ሳይዙ ሸቀጦችን ጭነው በሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
በሚኒስቴሩ የታክስ ማጭበርበርና ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ገዙ እንደገለጹት÷ የታክስ ሕጉ ማንኛውም ነጋዴ ወይም አገልግሎት ሰጪ ግብይት ካከናወነ በኋላ ደረሰኝ እንዲቆርጥ ቢያስገድድም ደረሰኝ የማይሰጡ አሉ፡፡
 
አንድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ሽያጭ በሚከናወንበት ጊዜ የተጨማሪ እሴት ታክስን 15 በመቶ ጨምሮ ከገዢው ወይም ከተጠቃሚው ለመንግስት ግብር እንዲሰበስብ በሕጉ ውክልና መሰጠቱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
 
ይሁንና በሀገራችን አገልግሎት ሰጪም ሆኑ በየደረጃው ያሉ የንግዱ ማህበረሰብ የታክስ ሕጉን ተከትለው እንደሚሠሩ ሁሉ ደረሰኝ የማይሰጡ መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
 
ከእነዚህ መካከል ሸቀጦች እና ንብረቶች የሚያጓጉዙ እና ጫኝ ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ሸቀጥ ከመጫናቸው በፊት ሕጋዊ ሰነድ መኖርና አለመኖሩን እያረጋገጡ መሄድ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
 
ይህንኑ ተቋሙ ወደ እርምጃ ከመግባቱ በፊት በማስታወቂያ እና በሌሎች የማስተማሪያ መንገዶች የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡
 
ሁሉም ክልሎች በዚህ ላይ በትኩረት እንዲሠሩ አቅጣጫ ለመስጠት መታሰቡን ጠቁመው÷ በየትኛውም ደረጃ ያሉ የሕግ አስከባሪ አካላት ጭነቶች በሚጓጓዙበት ጊዜ ህጋዊ ሰነድ መያዛቸውን እንዲያረጋግጡ እንደሚደረግም አብራርተዋል፡፡
 
በታክስ ሕጉ መሰረት አንድ ጭነት ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖረው ሲንቀሳቀስ ከተያዘ በዋናነት የጭነቱ ባለቤት ሸቀጡን ከየት እንዳመጣ ማስረጃ መስጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
 
ይህ ሳይሆን ሲቀር ወደ ኋላ በመሄድ ሸቀጡን ያለደረሰኝ የሸጠው አካል ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እና የሕግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትልበት መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.