Fana: At a Speed of Life!

ስለ ኃሞት ጠጠር አጋላጭ ምክንያቶች፣ ምልክቶች እና ሕክምና ምን ያህል ያውቃሉ?

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኃሞት ከረጢት (ፊኛ ) ጠጠር ወይም በተለምዶ የኃሞት ጠጠር የሚባለው በኃሞት ፊኛ ውስጥ ጠጠር ሲከማች ነው።

ይህ ጠጠር ለምን እና እንዴት እንደሚፈጠር የተለያዩ መላምቶች ሲቀርቡ ይስተዋላል፡፡

ከመላምቶቹ መካከል÷ የኮሊስትሮል በኃሞት ውስጥ መብዛት፣ ቢሉሩቢን በኃሞት ውስጥ መብዛት እና የኃሞት ፊኛ በውስጡ የሚገኘውን የኃሞት ፈሳሽ ወደ አንጀት መግፋት አለመቻል የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በአብዛኛው ለኃሞት ጠጠር ሕመም የሚጋለጡትም÷ ከጾታ አንጻር በአብዛኛው ሴቶች ተጋላጭ ናቸው፡፡

ከዕድሜ አኳያም ከ40 ዓመት በላይ መሆን እንዲሁም የሰውነት ክብደት መጨመር፣ የሌሎች ተጓዳኝ ሕመሞች (ለምሳሌ እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት) መኖር ለኃሞት ጠጠር ሕመም ተጋላጭ ያደርጋሉ፡፡

እንዲሁም የተለያዩ መድኃኒቶች ለምሳሌ የሚዋጥ የወሊድ መቆጣጠሪያ፣ ኮሊስትሮልን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ መድኃኒቶች እና ቤተሰብ ውስጥ የኃሞት ጠጠር ያለበት ሰው መኖር ይጠቀሳሉ፡፡

የኃሞት ከረጢት አብዛኛውን ጊዜ ምንም አይነት ምልክት እንደማያሳይ እና የሚታወቀው ለሌላ በሽታ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት መሆኑን የጥቁር አንበሳ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል፡፡

ምልክት ካሳየ ግን ዋነኛ የሚሆነው የሆድ ሕመም መሆኑና ሕመሙም የመውጋት ስሜት እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡

ይህም ብዙ ጊዜ ቅባታማ ምግቦችን ከመመገብ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ነው መረጃው ያመላከተው፡፡

በተጨማሪም ማስታወክ፣ ማቅለሽለሽ እና ትኩሳት የኃሞት ጠጠር ምልክቶች ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ።

የኃሞት ጠጠር ሕክምና ምልክት ካላሳየ ቋሚ ክትትል ከማድረግ ውጪ ሌላ ሕክምና የለውም፡፡ ምልክት ካሳየ ግን የቀዶ ሕክምና ማድረግ መፍትሔ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.