የሀገር ውስጥ ዜና

በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 248 ሺህ 300 ዶላር ተያዘ

By Meseret Awoke

December 29, 2022

አዲስ አበባ፣ ታኀሣሥ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንድ የቤት መኪና ዳሽ ቦርድ ውስጥ ተደብቆ በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 248 ሺህ 300 የአሜሪካ ዶላር ተያዘ፡፡

መነሻውን አዲስ አበባ ያደረገ አንድ የቤት መኪና ዳሽ ቦርዱ በስውር 248 ሺህ 300 ዶላር እንዲቀመጥበት ተደርጎ መዳረሻዉን ምስራቅ ሀረርጌ አድርጎ ጉዞ መጀመሩን የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።

የቤት መኪናው ከጅምሩ በደኀንነት ተቋሙ አይን ክትትል ስር ስለነበረ ለኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጥቆማ እንዲደርስ መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም አዳማ ከተማ ላይ የመኪናዉ ዳሽ ቦርድ እንዲበረበር ተደርጎ ዶላሩ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።

የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎትና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በመቀናጀት በቁጥጥር ስር ያዋሉት የአሜሪካ ዶላር ከሁለት አዘዋዋሪዎች ጋር ነው የተያዘው።

ህገወጥ ተግባሩን ከምንጩ ለማድረቅም  በአዲስ አበባና በምስራቅ ሐረርጌ ክትትላቸዉን መቀጠላቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተላከው መረጃ ያመላክታል።