Fana: At a Speed of Life!

የላሊበላ ከተማ ለልደት እና ገና በዓል እንግዶቿን መቀበል ጀመረች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በያዝነው ወር መጨረሻ በላሊበላ ከተማ ለሚከበረው የልደት እና ገና በዓል አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ እንግዶች ወደ ከተማዋ መግባት ጀምረዋል፡፡
የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ለበዓሉ ታዳሚ እግዶች የሚመጥን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል፡፡
ለበዓሉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ እንግዶች እንደሚጠበቁ ጠቁመው÷ ለእንግዶች ማረፊያ 45 ሆቴሎችን ጨምሮ አራት ትምህርት ቤቶች፣የቅዱስ ላሊበላ ገዳም ግቢ እና ድንኳን የሚጣልባቸው ሌሎች ቦታዎች ተሠናድተዋል ነው ያሉት፡፡
የንጹህ መጠጥ ውኃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሟላቱን፣ የመስኅብ አካባቢዎችና ከተማዋ ለጎብኚ ጽዱና ምቹ መሆናቸውን፣ ጊዜያዊ የመጸዳጃ ቤቶች መዘጋጀታቸውን እንዲሁም በቂ የጸጥታ ዝግጅት ተደርጎ ስምሪት መሰጠቱን አስረድተዋል።
ወደ ከተማዋ በሚያስገቡ ሰባት ኮሪደሮች የጎብኚውን ፍሰት ለመከታትል ስምሪት መሰጠቱንም ነው የተናገሩት።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሽ ግርማ በበኩላቸው÷ ሚኒስቴሩ በዓሉን ለማስተዋወቅ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ከመሥራቱ በተጨማሪ ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች ሌሎች የመስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ፓኬጅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የልደት እና ገና በዓል አከባበርን ብቻ ዐይተው እንዳይሔዱ በአካባቢው የሚገኙትን ይምርሐነ ክርስቶስ፣ አሸተን ማርያም፣ ነአኩቶ ለአብን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ መስኅቦችን እንዲጎበኙ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ ለአስጎብኚ ድርጅቶች መሰጠቱን እና በተለያየ የመገናኛ አውታር የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከማስተባበር በተጨማሪ ጊዜያዊ የመጀመሪያ ዕርዳታ ሕክምና መስጫ ማዕከላት እንዲቋቋሙ መደረጉን እና ከመደበኛው በተጨማሪ የአውሮፕላን በረራዎች እንዲኖሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ከስምምነት መደረሱንም ጠቅሰዋል።
በበዓሉ ላይ ለታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ለሚኒስትሮች፣ ለተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት አምባሳደሮች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ጥሪ ቀርቦ ምላሻቸውን እያሳወቁ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በግጭቱና በኮቪድ-19 ምክንያት ላለፉት ዓመታት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ፣ ጎብኚዎችን በአዲስ መልክ ለመሳብ፣ የማህበረሰቡን ኑሮ ወደነበረበት ለመመለስ ክብረ በዓሉ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል።
ከዚህ አንጻርም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል፣ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ እንዲሁም የውጭው ዓለም ማህበረሰብ ገናን በላሊበላ ተገኝተው እንዲያከብሩ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃንም በላሊበላ ከተማ የሚከበረውን የልደት እና ገና በዓል እንዲሸፍኑም ነው የጠየቁት።
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.