በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢኒስቲትዩቱ ዳይሬክተር አቶ ታምራት ቦጋለ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በክልሉ የወባ በሽታ ወረርሽኝ በሁሉም ዞኖች በ42 ወረዳዎች መከሰቱን አስታውሰዋል፡፡
ቤንች ሸኮ ዞንና ሸካ ዞን ደግሞ ከሌሎች ዞኖች አንፃር ከፍተኛ የህሙማን ቁጥር የተመዘገበባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሰዎች የወባ በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም በክልሉ የወባ በሽታ ወረርሽኝ መሆኑ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የመከላከል ስራዎች መሰራታቸውንና አሁንም እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ለአብነትም የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ጨምሮ አጎበርን ለህብረተሰቡ የማዳረስ፣ የኬሚካል ርጭትና ንቅናቄዎች መደረጋቸውን ጠቅሰው የኬሚካል እጥረት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡
ሆኖም በክልሉ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች የወባ በሽታ ስርጭት በተወሰኑ አካባቢዎች ቢቀንስም በቂ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።
በዚህም በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ከፌደራል ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ከአንድ ወር በፊት ባወጣው ሪፖርት መሰረት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በአማራ ክልል በልማት ቀጠናዎች አካባቢ፣ በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች፣ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ከፍተኛ የወባ ህሙማን ቁጥር ሪፖርት ተደርጓል፡፡
በፌቨን ቢሻው