የሀገር ግንባታን በፅኑ መሠረት ላይ ለማቆም ምሁራን በእውቀት የታገዘ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል- አቶ ብናልፍ አንዷለም
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር ግንባታን በፅኑ መሠረት ላይ ለማቆም ምሁራን በእውቀት የታገዘ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ፡፡
“በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ብናልፍ አንዷለም የሀገር ግንባታን በፅኑ መሠረት ላይ ለማቆም ምሁራን በእውቀት የታገዘ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
የሀገር ግንባታ በምሁራን ንቁና ጠንካራ ተሳትፎ ሊመራ እንደሚገባም መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከምሁራን ጋር በመመካከር እየሠራ እንደሚገኝ ማንሳታቸውን የአሚኮ ዘገባ ያመላክታል።
ሀገራት ያደጉትና የበለፀጉት በምሁራን ሀሳብ አመንጭነት መኾኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ምሁራን በውይይት መግባባት በመፍጠር በኩል ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ታላቅ የስልጣኔና የነፃነት ምልክት መኾኗን የተናገሩት አቶ ብናልፍ፥ አሁንም ሰላማዊና የበለፀገች ሀገር እንድትኾን ሁሉም ምሁር ሀሳብ በማፍለቅ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።
ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ዜጎች የፀናና የማይዋዥቅ አቋም እንዲይዙ ምሁራን በታሪክና በመረጃ በመመርኮዝ የማወያየትና የማግባባት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ ምሁራንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።