ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የሳዑዲ አረቢያውን አል-ናስር ተቀላቀለ
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፖርቹጋላዊ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የሳዑዲ አረቢያውን ክለብ አል ናስርን ተቀላቀለ።
የ37 አመቱ ሮናልዶ ከእንግሊዙ ማንቼስተር ዩናይትድ ጋር ከተለያየየ በኋላ አል ናስርን ለመቀላቀል መስማማቱ የሚታወስ ነው።
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲያያዝ ቢቆይም የመጨረሻ ማረፊያው የሳዑዲው ክለብ ሆኗል።
ሮናልዶ ለክለቡ ለሁለት አመት የሚያቆየውን ውል የፈረመ ሲሆን፥ ክለቡ 175 ሚሊየን ፓውንድ አመታዊ ክፍያ ለመክፈል መስማማቱ ነው የተገለጸው።
ሮናልዶ በክለቡ ከሚኖረው የሁለት አመታት የተጫዋችነት ቆይታ በኋላ የክለቡ አምባሳደር በመሆን ለመስራት መስማማቱን የሳዑዲ ምንጮችን ዋቢ ያደረገው የደይሊ ሜይል ዘገባ ያመላክታል።
በክለብ አምባሳደርነት ቆይታውም ሳዑዲ አረቢያ የ2030 የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ የምታደርገውን ጥረት ያግዛል ተብሏል።