ሰሞኑን የሚስተዋለው ቅዝቃዜ እስከ ጥር ወር መጨረሻ ሊቀጥል እንደሚችል ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰሞኑን የሚስተዋለው ቅዝቃዜ እስከ ጥር ወር መጨረሻ ሊቀጥል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ የምርምር ክፍል ዴስክ ኃላፊ ሙሉዓለም አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ሰሞኑን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመደበኛው ለየት ያለ ቅዝቃዜ እየተስተዋለ ነው።
ቅዝቃዜው አዲስ አበባን ጨምሮ ከባህር ጠለል በላይ ከ2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ሥፍራዎች ላይ የሚስተዋል መሆኑን ጠቅሰው፥ እነዚህ ሥፍራዎች የሌሊትና ማለዳ እንዲሁም የምሽት ቅዝቃዜ ተስተውሎባቸዋል ብለዋል።
አሁን ላይ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ፣ በደብረ ብርሃን፣ በሃሮማያ፣ በደቡብ ከፍተኛ ሥፍራዎች እንዲሁም በመካከለኛውና ሰሜን ምስራቅ የሚገኙ ከፍተኛ ሥፍራዎች ላይ ቅዝቃዜው በርትቷል ነው ያሉት።
ለቅዝቃዜው ዋነኛ መነሻው ከምስራቅ አውሮፓ ተነስቶ የአረቡን መሬት አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ቀዝቃዛና ደረቅ አየር መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህ አየር በሚገባበት ጊዜም አዲስ አበባን ጨምሮ 2 ሺህ 500 ወይም 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያላቸው ቦታዎች ላይ የሌሊት እና የማለዳው እንዲሁም የምሽት ቅዝቃዜው እንዲጨምር እንደሚያደርግም አስረድተዋል።
ይህም ቅዝቃዜ ለቀጣይ አንድ ወራት በመካከለኛው፣ በምስራቅና በደቡብ የሀገሪቱ ከፍተኛ ሥፍራዎች ላይ እንደሚቀጥልና የመጠናከር ባህሪ ሊኖረው እንደሚችልም የአየር ትንበያን ጠቅሰው አመላክተዋል።
ኅብረተሰቡም ቅዝቃዜውን ከግምት በማስገባት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አሳስቧል።