Fana: At a Speed of Life!

በሶሪያ የሠፈሩ የቱርክ ወታደሮች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ሥምምነት ላይ ተደረሰ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞስኮ የተካሄደውን የሦስትዮሽ ውይይት ተከትሎ ቱርክ ወታደራዊ ኃይሏን ከሰሜን ሶሪያ ግዛት ሙሉ በሙሉ ለማስወጣት መስማማቷ ተገለጸ፡፡

ወታደሮቹ ከቀጣናው ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ ሥምምነት ላይ የተደረሰው ቱርክ ፣ሶሪያ እና ሩሲያ በሽብርተኝነት እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በሞስኮ ከተነጋገሩ በኋላ መሆኑን አርቲ ዘግቧል፡፡

በፈረንጆቹ 2011 በሶሪያ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የቱርክ መከላከያ ሚኒስትር ሁሉሲ አካር ፣ የሶሪያው መከላከያ ሚኒስትር አሊ ማሃሙድ አባስ እና የሩሲያው አቻቸው ሰርጌይ ሾይጉ በሞስኩ ተገናኝተው ሲመክሩ በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡

የቱርክ እና የሶሪያ መከላከያ ሚኒስትሮች ÷“ዋይፒጂ” እና “ፒኬኬ” ብለው ራሳቸውን የሚጠሩት በሶሪያ እና ቱርክ የመሸጉ የኩርድ አማፂያን በውጪ ኃይል የሚደገፉ የጋራ ጠላት መሆናቸው ላይም ተመሳሳይ አቋም መያዛቸው ተገልጿል፡፡

ሀገራቱ በሞስኮ የደረሱባቸው ስምምነቶች መከበራቸውን ለማረጋገጥም ልዩ የሦስትዮሽ ኮሚሽን እንደሚያዋቅሩ ተጠቁሟል፡፡

የቱርኩ መከላከያ ሚኒስትር ሁሉሲ አካር እንዳሉት ሁሉም ነገር በአንድ ንግግር የሚፈታ ሳይሆን ሂደት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡

ሁሉሲ አካር አክለውም “የሶሪያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊ እናከብራለን፣ ዋና ግባችን ሽብርተኝነትን መዋጋት ብቻ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

“ፒኬኬ” ፣ “ዋይፒጂ” እና “አይ ኤስ” የተሰኙ የሽብር ቡድኖችም የጋራ ጠላቶቻችን ናቸው ማለታቸውም በዘገባው ተመላክቷል፡፡

በቀጣይ በሀገራቱ መካከል ሞስኮ ላይ የወረደው ዕርቀ-ሠላም ሥር እንዲሰድ ሉዓላዊነታቸውን ባከበረ መልኩ በአሸባሪነት የፈረጇቸው አማፂያን ላይ በጥምረት እርምጃ ለመውሰድ ይመክራሉም ነው የተባለው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.