የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አንደኛ መደበኛ ጉባዔውን “ለኢትዮጵያ እና አፍሪካዊ ብልጽግና የሚተጋ ወጣት” በሚል መሪ ሐሳብ በአዳማ ከተማ እያካሔደ ነው፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማኅበራት ዘርፍ ኃላፊ ዓለሙ ስሜ በጉባዔው ላይ የተገኙ ሲሆን÷ የሊጉ ፕሬዚዳንት አስፋው ተክሌን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።
በጉባዔው ላይ አቶ አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር÷ ብልጽግና ፓርቲ ባከናወነው አካታች ሥራ የወጣቶች ተሳትፎ በፓርቲው 51 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶች ወደ ፓርቲው መካተታቸው የወጣቶችን መብትና ጥቅም እንዲያስከብሩ ይረዳቸዋል ነው ያሉት።
እንዲሁም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሊጉን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡
አቶ አስፋው ተክሌ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ወጣቶች ብርቱ ተጋድሎ ማድረጋቸውን አስታውሰው÷ በተጨማሪም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በሌማት ትሩፋት እና በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች የማይተካ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ከኢትዮጵያ በተጨማሪ አህጉራዊ እንቅስቃሴን ለማጠናከር እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡
ጉባዔው በቆይታው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡
በሳሙኤል ወርቃየሁ