Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ጎንደርና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ10 ሰዎች ሕይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ጎንደር እና በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ፡፡

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ትናንት ከአመሻሹ 11፡30 ገደማ በደረሰው የትራፊክ አደጋ የአምስት ሰዎች ህይዎት አልፏል፡፡

በተመሳሳይ ደቡብ ጎንደር ደብረታቦር ከተማ በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 1፡00 አካባቢ ህሩይ አባረጋይ ቀበሌ ጃንሜዳ ማደያ አካባቢበደረሰ የትራፊክ አደጋ የአምስት ሰዎች ህይዎት አልፏል፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞኑን ባቢሌ ወረዳ ጃለሌ ቀበሌ ኦክሰን ሰፈር ሁለት የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ተጋጭተው በህይዎትና በሁለት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል፡፡

የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎቹ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርካር እርስ በርሳቸው በመጋጨታቸው የደረሰ አደጋ መሆኑንም ነው ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ የገለጹት፡፡

አሽከርካሪዎቹ ለጊዜው ከአካባቢው መሰወራቸውንና ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በደብረታቦር ከተማ ባጃጅ የተነሳው ወደጋሳኝ ሲሄድ እና ከጋሳኝ መስመር ወደ ደብረታቦር ከሚመጣ አይሲዩዙ መኪና ጋር ተጋጭተው በባጃጁ ውስጥ ከነበሩት ሹፌሩን ጨምሮ ሰባት ሰወች መካከል ነው አምስት ሰዎች ለህልፈት የተዳረጉት፡፡

እንዲሁም በንብረት ላይም ጉዳት የደረሰ መሆኑን ከደብረታቦር ከተማ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.