በየካ ክ/ከተማ ሾላ ገበያ በደረሰ የእሳት አደጋ 50 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ሾላ ገበያ በደረሰ የእሳት አደጋ 50 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብር መውደሙን የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ትናንት ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በሾላ ገበያ ማዕከል ከሚገኙ 1 ሺህ 600 ሱቆች ውስጥ 84 የሚሆኑት ላይ የእሳት አደጋ ደርሷል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ርብርብ ወደ ሌሎች ተዛምቶ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ አደጋውን መቆጣጠር መቻሉን ጠቁመው ÷ ከ1 ሺህ 516 የሚሆኑ የንግድ ሱቆችን ማትረፍ ተችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም 500 ሚለየን ብር የሚገመት ንብረት ከአደጋው ማትረፍ መቻሉን ነው አቶ ንጋቱ የተናገሩት፡፡
አደጋውን ለመቆጣጠር 12 የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች እና 95 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የተሰማሩ ሲሆን÷ አደጋውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር 4 ሰዓት 28 ደቂቃ መውሰዱ ተጠቁሟል፡፡
በአደጋው እስካሁን በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ጠቁመው÷ የአደጋ መንስኤም እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ