የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ቅዳሜና እሑድ በደረሱ ድንገተኛ አደጋዎች የ4 ሰዎች ሕይወት አለፈ

By Melaku Gedif

January 02, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ቅዳሜ እና እሑድ በደረሱ ድንገተኛ አደጋዎች የአራት ሰዎች ሕይወት አልፏል።

በከተማዋ ከደረሱት አደጋዎች ውስጥ አራቱ የእሳት አደጋዎች ሲሆኑ ÷ ቀሪዎቹ ደግሞ ከእሳት ውጪ ያጋጠሙ መሆናቸውን የአዲስ አበባ የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ቅዳሜ ዕለት በየካ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ቀርሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተቆፍሮ ክፍቱን በተተወና ውሀ ባቆረ ጉድጓድ ውስጥ የ14 ዓመት ታዳጊ ገብቶ ሕይወቱ ማለፉን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ቀን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ አካባቢ በሚገኝ ዛፍ ላይ ዕድሜው 32 ዓመት የሆነ ሰው ተሰቅሎ ህይወቱ ማለፉን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ቅዳሜ ሌሊት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወሎ ሰፈር አካባቢ ሱዙኪ የቤት አውቶሞቢል የመንገዱን አካፋይ ጥሶ በመግባት ለህንጻ ግንባታ የተቆፈረ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ በመግባቱ በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ 2 ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል፡፡

ቅዳሜ እና እሑድ በአቃቂ ቃሊቲ፣ ቦሌ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች በደረሱ የእሳት አደጋዎችም 975 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት የወደመ ሲሆን ÷ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉም ተመላክቷል፡፡

 

 

በመላኩ ገድፍ