Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ ለገና በዓል የምርት እጥረት እንዳያጋጥም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የገና በዓልን የምርት አቅርቦትን አስመልክቶ ከፌዴራል ህብረት ስራ ኮሚሽን ፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን እና ከንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ፍላጎት ስለሚጨምር የአቅርቦት ክፍተት እንዳይፈጠርና ህብረተሰቡ ላልተገባ ዋጋ እንዳይጋለጥ ሚኒስቴሩ ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ መስከረም ባህሩ ÷ የግብርና ምርቶች፣ የእንስሳት ውጤቶች እና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እቅርቦት እጥረት እንዳይኖርና ማህበረሰቡ ላልተገባ ዋጋ ጭማሪ እንዳይጋለጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ በበኩላቸው÷በአዲስ አበባ 137 ሸማች ማህበራት በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ ኤግዚቢሽንና ባዛር ማካሄዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በቅዳሜና እሁድ ገበያ ማዕከላት ምርቶች እየቀረቡ በመሆኑ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት እንዲሸምትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሽንኩርት ከ15 እስከ 22 ብር፣ ቲማቲም ከ15 እስከ 23 ፣ጤፍ 44 እስከ 49፣ስንዴ ዱቄት በኪሎ 55 ብር፣ በቆሎ ዱቄት 33፣ ዶሮ ከ350 እስከ 500 ብር በህብረት ስራ ኮሚሽን በኩል እየቀረቡ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከ161 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች ወደ ገበያ መቅረባቸውን የገለፁት አቶ አብዲ÷ ከ225 በላይ የህብረት ስራ ማህበራት ልኳንዳ ቤቶች በዓሉን በማስመልከት በተመጣጣኝ ዋጋ ስጋ እንደሚያቀርቡ አመላክተዋል፡፡

ከ100 ሺህ አስከ 150 ሺህ ኩንታል ስኳር በዓሉን ምክንያት በማድረግ በመላ ሀገሪቱ እየተሰራጨ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የስኳር ኮርፖሬሽን ማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ አቶ ታፈሰ አሰፋ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር እየተሰራጨ መሆኑንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

43 ሚሊየን ሊትር ዘይት ግዥ መፈፀሙንና ከዚህ ውስጥም 5 ሚሊየን ሊትር የሚሆነው እየተጓጓዘ መሆኑ ነው የተገጸው፡፡

ከዋጋ አንጻርም ባለ3 ሊትር  ዘይት 314ብር፣ ባለ 5 ሊትር  509 ብር፣ ባለ 20 ሊትር በ2 ሺህ 1 ብር ለገበያ መቅረቡ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.