የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ለገና እና ጥምቀት በዓላት አስፈላጊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው

By Meseret Awoke

January 03, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኀሣሥ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለመጪዎቹ ገና እና ጥምቀት በዓላት አስፈላጊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆኑን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት ለገና እና ጥምቀት በዓላት የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎችን አቅርቦት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ለበዓሉ የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ መሠረትም በክልሉ ሁሉም ዞኖች በንግድ ስርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚቆጣጠር ኮሚቴ ተዋቅሮር ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል።

ለገና እና ጥምቀት በዓላት በክልል ደረጃ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ እዘይት ለገበያ መቅረቡን አንስተዋል።

ከዋጋ አንጻርም 5 ሊትር ዘይት 840 ብር በላይ ይሸጥ የነበረው ለበዓላቱ ከ522 ብር ጀምሮ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ለበዓላቱ 38 ሺህ ኩንታል ስኳር ለገበያ መቅረቡን የገለጹት ሃላፊው፥የአንድ ኪሎ ዋጋም ከ57 ብር እስከ 67 ብር እንዲሸጥ መወሰኑን ጠቁመዋል።

680 ሺህ በላይ የእርድ እንስሳትም ከአቅራቢዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ለገበያ መቅረባቸውን ነው የተናገሩት።

ሽንኩርት፣ እንቁላል፣ ዶሮ ፣ስንዴ ዱቄት እና ሌሎች ግብዓቶችንም 102 የሚደርሱ የእሁድ ገበያ ማዕከላትን በማዘጋጀት ሸማቹ ከአርሶ አደሩ እና አምራቹ በቀጥታታ እንዲገዛ መደረጉን አስረድተዋል።

በዓላቱን ተከትሎ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በሁሉም ዞኖች የተዋቀረው ኮሚቴ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አቶ ዳንኤልአስረድተዋል።

ማህበረሰቡም ለበዓላቱ በቂ አቅርቦት መኖሩን ተገንዝቦ በተረጋጋ ሁኔታ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ጠይቀዋል።

በየአካባቢው ለምርቶቹ ከተወሰነው የመሸጫ ዋጋ በላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ሲመለከትም ለሚመለከተው አካል እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል።

በመላኩ ገድፍ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!