Fana: At a Speed of Life!

በህገወጥ መንገድ የይዞታ መብት በማጽናት የመንግስት ባዶ ቦታን በወሰዱና እንዲወሰድ ባደረጉ ግለሰቦች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገወጥ መንገድ በአርሶ አደርና በአርሶ አደር ልጅ ስም የይዞታ መብት በማጽናት የመንግስት ባዶ ቦታን በወሰዱ እና እንዲወሰድ ባደረጉ 21 ግለሰቦች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚን ጨምሮ በ21 ግለሰቦች በአርሶ አደርና በአርሶ አደር ልጅ ስም ለ11 ግለሰቦች ካርታ በማዘጋጀት 5 ሺህ 593 ካሬ ሜትር ይዞታን መብት በማፅናት እና አማካይ የሊዝ ዋጋው ከ11 ሚሊየን ብር የሆነ የመንግስት ባዶ ቦታን ወስደዋል እና እንዲወሰድ አድርገዋል በሚል ነው ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው፡፡

በዛሬው እለት ክስ የተመሰረተባቸው ተክሳሾች የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መልካሙ በቃናን ጨምሮ ሌሎች በተለያየ የአመራርነት እና በባለሙያነት እያገለገሉ የሚገኙ ግለሰቦች ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር በ2012 ዓ.ም በተለያዩ ቀናት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያወጣውን መመሪያ ቁጥር 4/2007 መሰረት የይዞታ ማረጋጋጫ የሚጠይቅ ሰው ማሟላት የሚገባውን መስፈርት ያላሟሉ፣ በህገወጥ መንገድ አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጅ ነን ያሉ 11 ግለሰቦችን የይዞታ ካርታ በማዘጋጀት አማካይ የሊዝ ዋጋው ከ11 ሚሊየን 900 ሺህ 67 ብር ከ31 ሳንቲም የሆነ የመንግስት ባዶ ቦታን በመስጠት፣ የካርታ መብት በማፅናት እንዲሁም 5 ሺህ 593 ካሬ ሜትር ይዞታን በህገወጥ መንገድ ወስደዋል ሲል ዐቃቤ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።

በአጠቃላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1 ሀ እና የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9/1 ሀ እና ንዑስ ቁጥር 2 በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባበብ በመጠቀም በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

ከተከሳሾቹ መካከል የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መልካሙ በቃና እና የክፍለ ከተማው የመሬት ማስከበር ጥበቃ ኦፊሰር ካርታ አረጋጋጭ ባለሙያ ገለታ ደበሌ ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በጽህፈት ቤት ከጠበቃቸው ጋር ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.