Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ጥቅሞችን ያሳድጋሉ የተባሉ 1 ሺህ 35 ደረጃዎችን ጸደቁ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ከጤና፣ ከአካባቢ ጥበቃና ንግድን ከማቀላጠፍ አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ያላቸውን 1 ሺህ 35 ደረጃዎች አጸደቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ ደረጃዎችን እንዲያዘጋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ዓለም አቀፍ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ያላቸውን ደረጃዎች አጸድቋል፡፡

ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ታኅሣሥ 19 ቀን 2015 ዓ ም ባካሔደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባ በሰባት ዘርፎች እና በ25 የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተዘጋጅተው ከቀረቡት 1 ሺህ 37 ደረጃዎች ውስጥ 1 ሺህ 35 ደረጃዎችን መርምሮ አጽድቋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የኢንስቲቱዩቱ ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ እንዳሉት÷ የጸደቁት ደረጃዎች ኢኮኖሚን ከማሳደግ፣ የሰውና የእንስሳት ደኅንነት ከማረጋገጥ፣ ከአካባቢ ጥበቃና ንግድን ከማቀላጠፍ አኳያ ሚናቸው ከፍተኛ ነው።

በተለይም የማምረቻውን ዘርፍ የንግድ ተወዳዳሪነት አቅምን ለማጎልበትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማከናወን እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

የደረጃው መጽደቅ የሸማቾችን ጥቅም ከማስጠበቅና የቁጥጥርና ክትትል ተግባራትን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጠር መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢንስቲቲዩቱ አስገዳጅ ደረጃዎች በትክክል ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል የክትትልና ድጋፍ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

ደረጃዎቹ በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ፣ በኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፣ በምግብና ግብርና ውጤቶች እንዲሁም በመሰረታዊ አጠቃላይ ደረጃዎች ተሰጥተዋል ነው ያሉት፡፡

በኮንስትራክሽንና ሲቪል ምህንድስና፣ በኤሌክትሮሜካኒካል ዘርፍና በአካባቢ ጤና ዘርፍ የተሰጡ ደረጃዎች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ በኮንስትራክሽን፣ በአካባቢ እና ጤና ደኅንነት፣ በዘይትና በለስላሳ መጠጥና በኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፍ 32 ደረጃዎች በአስገዳጅነት የጸደቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.