Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ እየተሠራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው የነበሩና ወደቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ወደልማት በማስገባት ከተረጂነት ለማላቀቅ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ወደቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ያለመ ሁለተኛ ዙር የመልሶ ማቋቋምና የምርት ዳሰሳ ጥናት ተጠናቆ ወደሥራ መገባቱን ገልጿል፡፡

የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ታረቀኝ ታሲሳ እንደገለጹት ፥ በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም የተተገበረው የመጀመሪያው ዙር ክልላዊ የዳሰሳ ጥናት ውጤት አምጥቷል፡፡

ኮሚሽኑ በጸጥታ ችግር ለተጎዱ ዜጎች ሠብዓዊ ዕርዳታ ከማድረስና በተፈጠረው አንጻራዊ ሠላም የተመለሱ ዜጎችን መልሶ ከማቋቋም ባለፈ በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ስትራቴጂክ ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ከ475 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ታረቀኝ ፥ በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊ ካምፕ ከሚገኙት 26 ሺህ ዜጎች ውጪ ሌሎቹ ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸውን አንስተዋል፡፡

ወደቀያቸው ከተመለሱት ዜጎች ውስጥ 345 ሺህ ለሚሆኑት የተጠናከረ ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑን መግለጻቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አቶ ታረቀኝ ፥ በቀጣይ ሠብዓዊ ድገፍ የማድረስና ወደቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ወደልማት በማስገባት ከተረጂነት የማላቀቅ ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር ርብርብ እንደሚደረግም ነው ያነሱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.