በ2023 መባቻ የአውሮፓ ሀገራት ያልተለመደ ሙቀት እያስተናገዱ ነው
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በያዝነው የፈረንጆቹ ዐዲስ ዓመት በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ያልተለመደ ሙቀት እያስተናገዱ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በአውሮፓ ያልተለመደው የጥር ወር ሙቀት መመዝገብ የጀመረው ሰሞኑን አሜሪካ በከባድ ቅዝቃዜ ተመትታ ከ60 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ መሆኑን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ዕሁድ ዕለት የተመዘገበው የፖላንድ የዓየር ንብረት የሙቀት መጠን 19 ነጥብ 9 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሲሆን ፥ ይህም ከዚህ ቀደም ከተመዘገቡት አማካይ ልኬቶች በ4 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንደሚልቅ ተመላክቷል፡፡
ከ15 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን ብዙም የማይዘለው የስፔን የዓየር ንብረት ፀባይ ደግሞ 25 ነጥብ 1 መድረሱ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ኔዘርላንድ፣ ሊችተንስታይን፣ ሊትዋኒያ፣ ላቲቪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፖላንድ፣ ዴንማርክ እና ቤላሩስ አስመዝግበው የማያውቁትን የሙቀት መጠን በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2023 ጥር ወር ላይ ማስመዝገባቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሌላ በኩል በአሜሪካ መካከለኛው ምዕራብ ከባድ በረዶ እና ቅዝቃዜ እንደሚቀጥል የዓየር ንብረት ትንበያዎች ሲያመላክቱ በቴክሳስ፣ ኦክላሆማ፣ አርካንሳስ እና ሉዊዚያና ነጎድጓዳማ እና አውሎ ነፋስ እንደሚጠበቅ ተዘግቧል፡፡