የሀገር ውስጥ ዜና

ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ አጋርነት አጠናክራ ትቀጥላለች – የሶማሊያ ፕሬዚዳንት

By Alemayehu Geremew

January 04, 2023

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ አጋርነት አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ገለጹ፡፡

የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት በሶማሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ ሀሰን በሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት በመገኘት ለፕሬዚዳንቱ የስንብት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት ያላት ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ኢትዮጵያ በፀረ ሽብር ዘመቻው ለሶማሊያ ባደረገችው ድጋፍ ያመሰገኑት ፕሬዚዳንቱ÷ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሠላም እና መረጋጋት ወሳኝ ሚና እየተጫወተች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ ሀሰን በቆይታቸው ስለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡