Fana: At a Speed of Life!

የገና በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገና በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የፊታችን ቅዳሜ ታህሳስ 29 የሚከበረው የገና በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ያደረገውን ዝግጅት በማስመልከት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ መግለጫ ሰጥተዋል።

የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው በቀጣይነት የሚከበሩትን ክብረ በዓላት ጨምሮ ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አስፈላጊው ሁሉ የጸጥታ ጥበቃ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ለሁነቶች የጸጥታ ግብረ ሃይሉ የ60 ቀናት እቅድ በማውጣት ወደ ስራ መግባቱንም ገልጸዋል።

በበዓላት ወቅት የሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች የወንጀል ሙከራዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቆሙት ምክትል ኮማንደር ማርቆስ በተለይም በገበያ ስፍራ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የትራፊክ ፓሊስ ከሚያደርገው ቁጥጥርና ክትትል በተጨማሪ አሽከርካሪዎች በጥንቃቄ በማሽከርከር ከአደጋ ተጠንቀቁ ሲሉም መክረዋል።

በየትኛውም አካባቢ አጠራጣሪ ነገሮች ሲጋጥሙ ህብረተሰቡ በየአቅራቢያው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች በግንባር በመቅረብ ወይም በስልክ ቁጥሮች 011-1-11-01-11 እና በ991 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.