በአማራ ክልል ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቅቀዋል- ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የገና በዓልን ጨምሮ በጥር ወር የሚከበሩ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን በሰላም ለማክበር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
በኮሚሽኑ የህብረተሰብ አቀፍና የመንገድ ላይ ትራፊክ ደህንነት ምክትል ዘርፍ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደረጀ አቻምየለህ እንደገለጹት÷ በዓላቱን በተሳካ መንገድ ለማክበር ተገቢ ዝግጅቶች ተደርገዋል።
መላ ህዝቡ ገና እና ጥምቀትን ጨምሮ ሌሎች ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን በሰላም እንዲያከበር ማህበረሰቡን ያሳተፈ የንቅናቄ መድረኮችን በመፍጠር ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
ከበዓላት አከባበር ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችን ቀድሞ በመለየት በብቃት መከላከል የሚያስችል ስምሪት መሰጠቱንም ጨምረው ገልፀዋል ኮሚሽነሩ።
ወንጀልን ለመከላከል ፖሊስ ብቻውን አይቻለውም ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ÷በመሆኑም መላውን ህብረተሰብ በተለይም ወጣቶችን ያሳተፈ የቅድመ ዝግጅት ስራ በስፋት መሰራቱን ተናግረዋል።
ለገና እና ጥምቀት በዓላት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ወደ ክልሉ የሚመጡ መሆኑን አንስተው÷እንግዶቹ ያለምንም የፀጥታ ስጋት በዓላቱን ማክበርና የቆይታ ጊዜያቸው እንዲያምር ተሰርቷል ብለዋል።
የሰላም ማስከበር ስራውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ መላ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆኖ ማገዝ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።
የፀጥታ ሃይሉ አስቀድሞ ተገቢውን ዝግጅት ያደረገ በመሆኑ ወደ ክልሉ የሚመጣ ማንኛውም ዜጋ በነጻነት በዓላቱን እንዲያከብር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ህብረተሰቡም ማንኛውንም አጠራጣሪ ጉዳይ ሲያጋጥመው በአቅራቢያው ለሚገኝ የፀጥታ ሃይል ፈጥኖ መረጃዎችን እንዲያደርስ ሲሉ ረዳት ኮሚሽነር ደረጀ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የክልሉ የገና በዓል በላልይበላ የጥምቀት በዓል ደግሞ በጎንደር በልዩ ዝግጅት በድምቀት የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።