የሃይማኖት አባቶች ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃይማኖት አባቶቹ የ2015 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
በመልዕክታቸውም÷ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የፍቅር እና የትህትና መሠረት በመሆኑ ክርስቲያን ምዕመኑ ርስበርስ በመፋቀር እና በመዋደድ በተግባር ሊተረጉመው ይገባል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች አሳስበዋል፡፡
እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ወደዚች ምድር መምጣቱ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ማሳያ በመሆኑ እኛም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያሳየውን ፍቅር ማሳየት ይገባናል ብለዋል።
ርስበርስ መዋደድ በሰላምና በፍቅር መኖር አምላካዊ ትእዛዝ ነውና በመንፈሳዊና አለማዊ የስራ ሃላፊነት የምንገኝ ሰዎች የእግዚአብሔር ትእዛዙን ማክበር ግዴታችን ነው ብለዋል።
በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በእግዚአብሔር እና በሰው ልጅ መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት መሆኑን አውስተዋል።
እናም በዓሉ የትህትና እና የፍቅር በዓል እንደመሆኑ ክርስቲያን ምዕመኑ በተለያየ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ እና ካለው በማካፈል በዓሉን አብሮ ማሳለፍ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በዕለት ዕለት እንቅስቃሴውም ለወገኑ በጎ ምግባራትን በማከናወን ኢየሱስ ክርሰቶስ ያሳየውን ተምሳሌትነት ሊተገብር ይገባል ብለዋል።
በቅድስት አባተ