የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
አቶ አደም ፋራህ በመልዕክታቸው በዓሉ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍስሀ፣ የቸርነትና የልግስና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ አቅመ ደካሞችን በመንከባከብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ በህግ ጥላ ስር ያሉ ወገኖችን በመጠየቅ እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡
አቶ አደም ያስተላለፉት የእንኳ አደረሳችሁ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለገና በአል በሰላም አደረሳችሁ።
በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍስሀ፣ የቸርነትና የልግስና እንዲሆንላችሁ ምኞቴ ነው።
በአሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችን በመርዳት፣ አቅመ ደካሞችን በመንከባከብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ በህግ ጥላ ስር ያሉ ወገኖችን በመጠየቅ፣ ቤታቸው የጎደለ ድሆችን አይዟችሁ በማለት፣ ካለን እና ቤታችን ካፈራው ላይ በማቋደስ፣ ፍፁም በሆነ መተሳሰብ በሞላው ኢትዮጵያዊ የጨዋነት መንፈስ ሊሆን ይገባል።
ይህን ማድረጋችን አንድም በፈጣሪ ዘንድ ቸሮታን የሚያስገኝልን ሲሆን አንድም ሰብአዊነትን በህብረተሰባችን ዘንድ በማሳደግ የሞራል ልእልናችንን ከፍ የማድረግ አቅም ስላለው ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በአሉን በመተሳሰብ እንድታከብሩት አደራ ማለት እፈልጋለው።
በተለይም ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆን አባል ያለው ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነው የብልፅግና ፓርቲ አባል የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን እናንተን በልዩ ሁኔታ አደራ ማለት የምፈልገው ይህንኑ ነው።
በበአላት ወቅት መረዳዳት መተሳሰብ እና መደጋገፍ ሰው ተኮር የሆነው የፓርቲያችንን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ያስችለዋልና በዚህ በአል ላይ በስፋት በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ላይ እንድትሳተፉ አደራ ማለት እፈልጋለው።
መልካምነት ክፍያው ብዙ ነውና፣ እንደ ብልፅግናም ልንገነባት የምንፈልጋት ሀገር መሰረቷ ሰብአዊነት ነውና ትኩረታችንን መረዳዳት እና መደጋገፍ ላይ አድርገን በአሉ በሀምራዊነት ተሸምነን የምንንፀባረቅበት፣ በቸርነትን እና በልግስና የሚገኘውን በረከት በጋራ የምንቋደስበት ሊሆን ይገባል።
ሌላው አደራ ማለት የምፈልገው ጉዳይ በፓርቲያችን ውስጥ በአመራርነት ደረጃ ላይ ያላችሁ ግለሰቦችን ነው። ይህ በአል ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር፣ በዋጋ ላይ የሚስተዋሉ ንረቶች እንዳይፈጠሩ፣ ድንገተኛ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የበአሉን ድባብ እንዳያደበዝዙት በከፍተኛ የሀላፊነት ስሜት እንድትንቀሳቀሱ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
በተመሳሳይም በአሉን ተከትሎ የሚፈጠሩ የበጎ አድራጎት ንቅናቄዎችን በአግባቡ እንድታስተባብሩ በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ይህ በአል የሚከበርበት ወቅት እንደ ሀገር የገጠሙንን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እየፈታን ባለንበት ሁኔታ ላይ ሆነን፣ የተስተጓጎሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን ዳግም እያስጀመርን፣ የሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን በከፍተኛ ጥረት ተደራሽ እያደረግን በምንገኝበት ሁኔታ ላይ ሆነን የሚከበር መሆኑም ልዩ ያደርገዋልና ይህንን በአል ተጠቅምን የተፈጠረውን የእርቅ መንፈስ ይበልጥ እንድናዳብረው፣ ይበልጥ እንድናሰፋው እጠይቃለሁ።