የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገና በዓልን ለማክበር ላሊበላ የገቡት የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝተዋል፡፡
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በገና በዓል ላይ ለመታደም ዛሬ ላሊበላ ከተማ መግባታቸው ይታወሳል፡፡
በጉብኝት መርሐ ግብሩ በቱሪዝም ሚኒስቴር ግብዣ ወደ ላሊበላ የተጓዙ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ከ10 በላይ አምባሳደሮችና ከ20 በላይ ሀገራት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
አምባሳደሮቹ በጉብኝት ወቅት በፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ መደነቃቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ስለ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ለመናገር በጣም ይከብዳል፤ ሲነገር የሚታየውን ያህል ሊሆን አይችልም ሲል የገለጸው በኢትዮጵያና ጅቡቲ የቤልጅየም አምባሳዶር ስቴፋን ቲጅስ ነው።
አምባሳደር ስቴፈን በአካባቢው የነበረው ግጭት ተወግዶ አካባቢው ለጉብኝት ክፍት መደረጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸው÷ በቀጣይም ቱሪስቶች ላሊበላን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላም ዳዊት በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት÷ መርሐ ግብሩ አካባቢው በኮቪድ -19ና በግጭቱ ምክንያት ጎብኚዎች እርቀውት ስለነበር ቱሪስቶች እንዲመለሱ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት ብዙ ሀገራት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አስታውሰው÷ አሁን ላይ አካባቢውን አይተው ሰላምነቱን በማረጋገጥ ማስጠንቀቂያውን እንዲያነሱ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በሜሮን ሙሉጌታና ታምሩ ከፈለኝ