Fana: At a Speed of Life!

በፍርድ ሂደት ላይ እያለ ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ያመለጠው ኪዳነ ዘካርያስ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቁጥጥር ሥር ውሎ በፍርድ ሂደት ላይ እያለ ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ፖሊስ እጅ ያመለጠው ኪዳነ ዘካርያስ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖለስ አስታወቀ፡፡

በስደተኞች ላይ በሚፈጽመው የጭካኔ ተግባርና ግፍ የተሞላበት አያያዝ የሚታወቀው አደገኛ የሰዎች አዘዋዋሪ ኪዳነ ዘካርያስ ሀብተማርያም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዓለም አቀፍ የፖሊስ ኅብረት ድርጅት (ኢንተርፖል) በኩል ባሰራጨው መረጃ መሠረት በሱዳን በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ተጠርጣሪው በምስራቅ አፍሪካ ስደተኞች ላይ ከሚደረገው አፈና፣ ዝርፊያ እና ግድያ ጀርባ ያለውን ትልቅ የወንጀለኛ ድርጅትን በመምራት በኢትዮጵያ እና በኔዘርላንድስ ስደተኞችን በህገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወርና በሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች በፈረንጆቹ ከ2019 ጀምሮ በሁለት የኢንተርፖል ቀይ ማስታወቂያዎች ይፈለግ እንደነበር ይታወቃል።

የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት፣ የዓለም አቀፍ የፖሊስ ኅብረት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ የኔዘርላንድስ ፖሊስ፣ ኢሮፖል እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በጋራ በመተባበር በአቋቋሙት ግብረ-ሃይል መካከል በተደረገው የመረጃ ልውውጥ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል÷ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ግብረ-ኃይሉ ሌት ተቀን ባደረጉት ብርቱ ክትትል በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አንስተዋል፡፡

ይህም ማንኛውም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ሊያመልጥ እንደማይችል ማሳያ እንደሆነ ተናግረው÷ የተጠርጣሪው መያዝ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ገልፀዋል።

ከምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅጽና ከኢንተርፖል አባል ሀገራት ጋር በመተባበር በተጠርጣሪው ዙሪያ እየተካሄዱ ያሉ ተጨማሪ ምርመራዎች የቀጠሉ ሲሆን÷ በዚህም ሌሎች በዓለም አቀፍ ደረጀ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ የተዘረጋውን የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ለመበጣጠስ ለጀመረው የተጠናከረ ኦፕሬሽን ኅብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን ሆኖ የተለመደውን ቀና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.